ሚድያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ
ሮይተርስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ዘገባ እንዳይሰራ ታገደ፡፡
መቀመጫውን አዲስ አበባ በማድረግ የዘገባ ስራ ለመስራት ፍቃድ የነበረው ሮይተርስ የስራ ፈቃዱን መነጠቁ ተነግሯል፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በሰሜኑ ክፍል እየተካሄደ ያለውን ውጊያ በተሳሳተ መንገድ አለም እንዲያውቀውና በኢትዮጵያ መንግስት ላይም ጫና እንዲበረታ በሚያደርጉ የሚዲያ ተቋማት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የብሮድካስት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን አንዷለም እንደተናገሩት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ በማድረግ ፈቃድ የተሰጣቸው የውጪ ሀገር ተቋማት ወቅታዊውን ሁኔታ በጥንቃቄና በሙያ ስነ ምግባር እንዲዘግቡ ማሳሰቢያ ብንሰጥም በእምቢተኝነት በቀጠሉት ላይ እርምጃ ወሰደናል ብለዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ በምሳሌነት ከጠቀሷቸውም ዶይቼ ቬለ፣ ቢቢሲና ሮይተርስ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷቸዋል ያሉ ሲሆን ሮይተርስ ግን ከድርጊቱ ሊታቀብ ባለመቻሉ ሀገር ውስጥ ያለው ዘጋቢ በምንም አይነት ሁኔታ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንቅስቃሴ እንዳታደርግና ዜናዎችንም ሆነ ዘገባዎችን እንዳትሰራ አግደናታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሀገር ውስጥ ባሉ የሚዲያ ተቋማትም ሆነ ለአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ፍቃድ ከመስጠት አንስቶ የሚዲያ ቁጥጥር ስራ ይሰራል ያሉት አቶ አንዷለም ትክክል ያልሆነና ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ስራዎችን በሚሰሩ ተቋማት ላይ የምናደርገው ቁጥጥር ወደፊትም ይቀጥላል ማለታቸውን ሸገር ዘግቧል፡፡
Credit: Mootii Oroo
No comments:
Post a Comment