የመቀሌ እፎይታና የህግ የማስከበር ስራችን ወሳኝ ውጤት
የህግ ማስከበር ተልእኮአችን ሶስተኛና ወሳኝ ምእራፍ የመቀሌ ከተማን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር የድል ብስራት እነሆ ተጀምሯል። መቀሌ የወንጀለኞችና የሃገርና ህዝብ ከሐዲዎች የግዳጅ ምሽግነትን ዛሬ በቃኝ ብላለች።
መቀሌ የትግራይ መላ ህዝቦችን ጉሮሮ ለ 45 አመታት አንቆ ንፁህ አየር መተንፈሻ ያሳጣቸውን ዘንዶውን የትህነግን ጁንታና አሸባሪ ድርጅት ፤ ጀግናውንና ሕዝባዊውን የመከላከያ ሰራዊታችንን የወጋበትን የክህደት ምሸት በድልና የእውነት ብርሐን ለማጋለጥ ተጣድፋለች።
መቀሌ የሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ገበያነቷ ያከትም ዘንድ ውሸት ፈጭተው ፣ ጥፋት አቡኩተውና ሞት ደግሰው የመለያያትና የጦርነት አስጨናቂ መልእክቶችን ከላንቃቸው የሚተፋትን የጥፋትና የክህደት ሃይሉን ሚዲያዎች ሙሉ በሙሉ ለሰፊው ህዝብ እውነተኛ ጥቅም ይውሉ ዘንድ ርክክብ ለመፈፀም አለሁኝ ብላለች።
አገራችን ባለፋት ሶስት ሳምንታት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሸት በመከላከያ ሰራዊታችን የሰሜን እዝ ላይ የትህነግ ጁንታ፣ ከጥቂት ሰርጎ ገብና የክብር መለዮአቸውን ካረከሱ ከሐዲ የመከላከያ ሰራዊታችን አባላትና ወታደራዊ መኮንኖች ጋር በማበር የፈፀሙትን መጠነ ሰፊ ጥቃት፤ በህግ የማስከበር ዘመቻ ለመቀልበስ በሶስት ምእራፎች ሲካሔድ የቆየው ወንጀለኞችን አድኖ የመያዝና በመላው ትግራይ ሰላምና ነፃነት የማስፈን ዘላቂ ተግባር በጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ፣የአማራ ክልል ልዮ ሐይልና ሚሊሺያ እንዲሁም ዳር እስከዳር በተንቀሳቀሱት የኢትዮጰያ ህዝቦች የጀግንነት የላቀ ተጋድሎ ወደ መዳረሻ ግቡ ተዳርሰዋል።
አገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ ካጋጠሙዋት ልዮ ልዮ የውስጥና የውጭ እንዲሁም ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች ውስጥ ይህ በአይነቱ የተለየ ነው። ወደፊት በሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ የታሪክ ፀሐፊዎች ጭምር የሚፈተሸው ፤ በሐገረ መንግስት ግንባታ የፌደራል ስርአት ትግበራ ወይንም በአጠቃላይ የስነ መንግስት ልምምዶች ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የክህደት ተግባር ተፈፅመዋል። ይህ በፈፀመው የህወሀት ጁንታ ላይ የሚወሰደው የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር የመንግስትን ምልአተ ትእግስት ያስመሰከረ ፣ ለዘመናት ለሀገር ዳር ድንበርና ሉአላዊነት መከበርና ለመስዋእትነት የከተተውን መከላከያ ሰራዊታችንን እጅጉን ያስቆጣ ፣ የአገራችንን ህዝቦች አንድነትና ትብብር ለወዳጅም ለጠላትም ለግፈኞችም ጭምር በአደባባይ ያሳየ መሆኑ ገና ብዙ ይነገርበታል።
በተለይም መላው የትግራይ ህዝብ በዚህ ግዜ ይህንን በልቡ ጠንቅቆ የሚያውቀውን እና በጭካኔው ዳፋ ለአመታት ያሰቃየውን ጁንታ፤ ለአመታት በሰራቸው ከፋፋይ ሴራዎቹ ወንድም ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ከመላው የአማራ ህዝቦችና የተቀሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ያለውን የማይበጠስ ትስስርና ግንኙነት በማዳከም ፣ የክህደት ግብሩንም በመፈፀም ፣ ለመከራ የዳረገውን ቡድንና ድርጅት በመጨረሻ ሰአትም እንኳን ለሰላም የተዘረጋለትን በትር በንቀትና እምቢተኝነት በማጣጣል፤ ከተደበቀበት ጎሬ ውስጥም ሆኖ በካራ የእጅ የነፍስ ወከፍ መሳርያ በዱላም ጭምር ከመከላከያ ሀይላችን ጋር እንዲፋለም በይፋ ጥሪ በማድረግ በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ ጨካኝ ተግባር መፈፀሙን በአይኑ አይቷል።
መቀሌን ከብቦ የነበረውን ሰራዊታችን ስም ለማጠልሸትና በሕዝቦች ላብና በመንግስት ሐብት የተገነባችውን የመቀሌ ከተማንና ነዋሪዎችዋን ምሽግ በማድረግ ፅኑ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም መንግስት የሰላማዊ ዜጎችን ሞት መጎዳት ንብረትና ሐብት ውድመት ኪሳራ በመቀነስ ከተማዋን ለመቆጣጠር በገባው ቃል መሰረትም ከሃያ አራት ሰአት ባልበለጠ ግዜ ከተማዋን ለመቆጣጠር ችሏል።
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በተቆጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎች የህዝቡ የሰላም ናፋቂነትና ድጋፍ በይፋ የታየ ከመሆኑም በላይ በልዮ ልዮ አካባቢዎችም መደበኛ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። በመቀሌ መሽጎ እንዳለ የሚገኘውን የጁንታውን ቡድን መላው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ከመከላከያ ሃይላችንና የመንግስት ልዮ የፀጥታ መዋቅሮች ጋር በትብብርና በቅርበት በመስራት እንዲያጋልጥና ለህግ በማቅረብም ከተማዋን ብሎም ትግራይን ወደ ሰላምዋ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በንቃት ሊያግዝ ይገባል።
ይህ ተስፋ ሰጪና ወሳኝ የህግ የማስከበር ተልእኮ ምእራፍ በቀጣይ ቀናት በከተማዋ ወደ ላቀ ውጤት በማሸጋገር መደበኛ የግንኙነትና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ፈጥኖ ወደ ነበሩበት ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎችም ከወዲሁ መሰራት ጀምረዋል ። የመብራት አገልግሎትን ከሁለት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት አየተደረገ ያለ ሲሆን የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶችንም በአጭር ቀናት ሙሉ በሙሉ ለማስጀመር የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል።
በመካሔድ ላይ ባለው የህግ ማስከበር ስራና የሎጂስቲክ መቋረጥ ሳብያ ባለፋት ቀናት በመቀሌ ከተማ እንዲሁም በአብዛኛው የትግራይ ከባቢዎች የምግብ የመድሐኒትና አስፈላጊ የህይወት አድን ስራዎችን ማከናወን አስቸጋሪ የነበረ መሆኑን ልዮ ትኩረት በመስጠት የሰብአዊ እርዳታና አቅርቦቶችን ተደራሽ የሚያደርግ ዝግጅት የዘመቻው አካል ተደርጓል።
መላው የመቀሌ ህዝብ የፌደራል ፖሊስ በከተማዋ የሚያደርገውን ወንጀለኞችን የማደን ዘመቻ ሰላምና መረጋጋትን የማስፈን የከተማ ፓትሮልና ህዝባዊ የጎዳና መልእክቶች ባለበት ቦታ ሆኖ በንቃት እንዲከታተል በቀጣይ ሰአታት ስራዎች ይሰራሉ።
ክብር ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን !
ፈጣሪ አገራችንና ህዝቦችዋን ይጠብቅ ይባርክ !
No comments:
Post a Comment